Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ የሳይበር ጥቃት ሲያደርስ የነበረ የሳይበር ወንጀለኛ ቡድን መሪ ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖልና በርካታ የሳይበር ደህንነት ተቋማትን ያካተተዉ “ኦፕሬሽን ደሊላ” ከአንድ ዓመት ምርመራና ክትትል በኋላ በናይጀሪያ መቀመጫዉን ያደረገዉን የሳይበር ወንጀለኞች ቡድን መሪ መያዙን ገለጸ።

በዓለም አቀፍ ዘመቻው የናይጄሪያ ፖሊስ ሃይል ተሳታፊ የነበረ ሲሆን ፥ ሲልቨር-ቴሪየር ወይም ቲኤምቲ በመባል የሚታወቀውንና በኢ-ሜይል አማካኘት ጥቃት የሚያደርሰዉ ቡድን መሪን በቁጥጥር ስር አውሏል።

ኦፕሬሽን-ደሊላ የሚል መጠሪያ በተሰጠዉ ሚስጥራዊ ዘመቻ የአራት አህጉራት የፖሊስ ተቋማትን ያሳተፈ ሲሆን ፥ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሲልቨር-ቴረር ቡድን አባል የሆኑ ተጠርጣሪዎችን በመለየትና በማሰር ላይ ያተኮረ ስራዎችን ሲሰራ እንደነበር ተጠቅሷል።

የሲልቨር-ቴረር እንቅስቃሴ እኤአ 2015 ጀምሮ ወደ ተግባር መግባቱን ያመለከተዉ የኢንተርፖል መረጃ ቡድኑ ፥ ግዙፍ የተባሉና በኢ-ሜይል የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶችንና መረጃ የማጥመድ ተግባራትን መፈጸሙን ጠቁሟል።

ወንጀለኞችን በማደን እንቅስቃሴ በሳይበር ተመራማሪዎች የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም የተንቀሳቀሱ ሲሆን ፥ ኦፕሬሽን ደሊላ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ የተሰማራዉ ትሬንድ ማክሮ የበኩሉን የወንጀለኖቹን እንቅስቃሴ፣ ቴሌሜትሪ መረጃና መሰል ወንጀለኞቹን ለመያዝ የሚያግዙ ኢንፎርሜሽኖችን በማቅረብ ላይ የራሱን አስተዋጽዎ አድርጓል።

“ኦፕሬሽን ደሊላ” በፈረንጆቹ በግንቦት 2021 የጀመረ ሲሆን ፥ በዚህ ኦፕሬሽንም የ37 ዓመቱን ናይጄሪያዊ ተጠርጣሪ ፣ በሌጎስ ሙርታላ መሃመድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር አዉሎታል።

“ኦፕሬሽን ደሊላ” በዓለም አቀፉ ፖሊስ ተቋም መሪነት የተከፈቱ (ፋልከን I- በፈረንጆቹ 2020 እንዲሁም ፋልከን II በ2021) ከተከናወኑ ዘመቻዎች ቀጥሎ የተከፈተ የሳይበር ወንጀለኞችን የማደን ዘመቻ መሆኑ ታውቋል።

ከኢንተርፖል ጋር በትብብር ሲሰሩ ከነበሩት የሳይበር ደህንነት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነዉ ግሩፕ-አይቢ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ሲልቨር-ቴረር የተባለዉን ቡድን ሲከታተል የቆየ ሲሆን ፥ ቡድኑ በፈረንጆቹ 2020 ብቻ በ150 ሃገራት ያሉ 500ሺህ ኩባንያዎችን የሳይበር ጥቃቱ ኢላማ አድርጎ መንቀሳቀሱን ገልጿል።

በአጠቃላይ በኢ-ሜይል አማካኝነት የሚፈጸሙ የማጭበርበር ተግባራት በአሁኑ ሰዓት ለወንጀለኞቹ አዋጪ ከሚባሉ የሳይበር ወንጀል መፈጸሚያ አማራጮች አንዱ ሲሆን ፥ከራንሰምዌር ጥቃቶች ከሚገኙ የበለጠ ትርፋማ መሆኑንና ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲሰራበት የቆየ ዘዴ ነዉ።

በዚህ ወንጀል ሳቢያም በፈረንጆቹ 2021 ብቻ ወደ 2ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ በተጎጂዎች ላይ እንደደረሰ ሪፖርት መደረጉን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.