Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሐፊ በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 5ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ፔሩያዊው ጃቬር ፔሬዝ በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ጃቬር ፔሬዝ ሊማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፥ ከላቲን አሜሪካ ድርጅቱን በዋና ጸሀፊነት በማገልገል ብቸኛው ተወካይ ናቸው።

ከፈረንጆቹ ከ1982 እስከ 1991 ለሁለት ጊዜ ድርጅቱን በዋና ጸሀፊነት ያገለገሉት ጃቬር ፔሬዝ፥ የኢራንና ኢራቅን ጦርነት በማስቆም ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወታቸው ይነገራል።

ከዚህ በተጨማሪም የቀዝቃዛው ጦርነት እንዲያበቃና ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲጎለብት መስራታቸውም ነው የሚነገረው።

ይሁን እንጅ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራቸው በ1990 የተቀሰቀሰውን የባህረ ሰላጤውን ጦርነት እንዲያስቆሙ አላደረጋቸውም።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፥ ፔሬዝ በሊባኖስ የሚገኙ የአሜሪካ ታጋቾችን በማስለቀቅ እና ካምቦዲያና ኤልሳልቫዶር የሰላም ስምምነት በማድረግ የሰሩትን ስኬታማ ስራ በማስታወስ አድንቀዋል።

አያይዘውም ፔሬዝ ተመድንና ዓለምን በመለወጥ ረገድ የተዋጣላቸው፣ ቆራጥ ዲፕሎማትና ተነሳሽነታቸው ከፍ ያሉ መሪ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ምንጭ፦ ሬውተርስ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.