Fana: At a Speed of Life!

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖራቸው የባለድርሻ አካላት ርብርብ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭትና ተፈጥሮ ክስተት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖራቸው የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ያለመና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ስብስባ በአዳማ እየተካሄደ ነው፡፡
በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና በስብሰባው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር÷ ጦርነት፣ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎች ክስተት በቀጠናው በርካታ ዜጎች ጥራት ያለውን ትምህርት እንዳያገኙ መንስኤ ሆኗል ብለዋል።
የስብሰባው ዓላማ በቀጠናው ውስጥም ሆነ ድንበር ተሻጋሪ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማመንጨት መሆኑንም ተናግረዋል።
በጦርነት፣ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈናቀሉ ዜጎች ምን ዓይነት ትምህርት በምን መልኩ ማግኘት እንደሚችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ “ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀልና መራቅ የለባቸውም” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
በሀገራችን የሰሜኑ ክፍል በጦርነት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ከበፊቱ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ተቋማቱን መልሶ የመገንባትና የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዶክተር ኤባ ያነሱት፡፡
ከትግራይ ክልል ውጭ የነበሩና በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ መማር- ማስተማር መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ስብሰባው በግጭቶችና በተለያዩ ምክንያቶች ከጎረቤት ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡና ከሀገራችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተፈናቅለው ያሉ ሕፃናትና ዜጎች በምን መልኩ ትምህርት ማግኘት እንደሚችሉም ጭምር የሚመክር ነው ተብሏል።
እንዲሁም አመቺ የሆነ ስርዓተ ትምህርት እንዲኖር ጭምር ለቀጠናው መንግስታት የፖሊሲ ግብዓት ሊሆን የሚችል ምክረ ሃሳብ የሚቀርብበት እንደሆነም አንስተዋል።
በተለይ የተፈናቀሉ ሕፃናት በሚችሉት ቋንቋ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት(ኢጋድ) እገዛ አማራጮች ይቀርባሉ ነው ያሉት።
ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ባህሪ ጥናት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ይቆይአለም ደሴ÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በተለያየ መልኩ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ በዘርፉ የተካሄዱ 32 የጥናት ወረቀቶችና 3 በፖሊሲ ዙሪያ ያጠነጠኑ ጽሑፎች ቀርበው እንደሚመከርበት ታውቋል።
ስብሰባው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ ባህሪ ኮሌጅና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን÷ በስብሰባው ከአሜሪካ፣ አውሮፓና የአፍሪካ ሀገራት በበይነ መረብ የተለያዩ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ስብሰባው ዛሬን ጨምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.