Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለተቋቋመለት አገራዊ አጀንዳ ተግባራዊነት ሁሉም የህብረተስብ ክፍሎች ቁርጠኛ ሆነው እንዲነሱ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለተቋቋመለት አገራዊ አጀንዳ ተግባራዊነትና ውጤታማነት ሕዝቡ፣ ሁሉም የህብረተስብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት የበለጠ ቁርጠኛ ሆነው እንዲነሱ ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዛሬ ወቅታዊ መልዕክት አስተላልፏል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የፖለቲካና የሀሳብ መሪዎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጕዳች ላይ የሀሳብ ልዩነትና አለመግባባት መኖሩ ይታወቃል ያለው ኮሚሽኑ፥ ሰፋፊ ሀገራዊ የሕዝብ ምክክሮች በየደረጃው አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ እነዚህን ልዩነቶችና አለመግባባቶች ለመፍታት እና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ኮሚሽኑ መቋቁሙን አስታውሷል።

ሦስት ወራትን ባስቆጠረ ዕድሜው፥ ውስጣዊ የአሰራር ድንጋጌዎችና መመሪያዎችን ከማውጣት ባሻገር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትውውቅ ማካሄዱን በመጠቆምም የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ መሆኑን አስታውቋል።

አገራዊ ሰላምና መረጋጋት ለምክክሩ ሂደት ትግበራ ስኬታማነት ወሳኝ በመሆኑ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰላም እናቶችና ወጣቶች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁሉም የአገራችን ዜጎች ከምንጊዜውም በተጠናከረ ሁኔታ አካባቢያዊና አገራዊ ዕርቅ ለማምጣት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላልፏል።

በየቦታው ያለው ግጭትና ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ሁሉም ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመጡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ወገኖችና ሰላም ወዳዱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርጉ ነው ኮሚሽኑ አበክሮ የጠየቀው።

በሌላ ወገን ሀሳብ አፍላቂዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሜዲያ ባለሙያዎች ስለሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት ለሕዝባችን ስለሚሰጡት ትምህርትና ማብራሪያ ኮሚሽኑ ከፍተኛ አክብሮቱንና ምስጋናውን የገለፀ ሲሆን፥ ኮሚሽኑ የተሻለ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በአካባቢው ቋንቋ ተደራሽ ለማድረግ በሚነድፈው መርሐ ግብር መሠረት አብረውት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።

ይህን አገራዊ አጀንዳ ተግባራዊ እና ውጤታማ ለማድረግ ሕዝቡ፣ ሁሉም የህብረተስብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት የበለጠ ቁርጠኛ ሆነው እንዲነሱም ኮሚሽኑ ጥሪ አድርጓል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.