Fana: At a Speed of Life!

በሻምቡ የተገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ የተገነባው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጁ አቶ አሸናፊ ሙሉብርሃን እንደገለጹት÷ማከፋፈያ ጣቢያው ለሻምቡ ከተማ እና ለአሊቦ ቀበሌ በአማካኝ ሁለት ሜጋ ዋት ኃይል እየሰጠ ይገኛል፡፡

ጣቢያው አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመር እና ስድስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንዳሉት ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

ከወጪ መስመሮቹ ሁለቱ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን አራቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን በመጠባበቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፈርመሮች፣ አንድ የኃይል መቆጣጠሪያ ክፍል እና የኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ ስርዓት አሉት ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱን ለመገንባት 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እና 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 85 በመቶው ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የቻይናው ሲኖ ሃይድሮ ኩባንያ በዋና ተቋራጭነት፤ ሀገር በቀሉ መላ ኢንጂነሪንግ የሲቪል ሥራውን በንዑስ ተቋራጭነት ሲያከናውኑት የጣሊያኑ ኢ.ኤል.ሲ ኤሌክትሮ ኮንሰልት ደግሞ የማማከር ሥራውን ማከናወኑ ተነስቷል ፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያ ለአካባቢው ማህበረሠብ እና የማምረቻ ፋብሪካዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡ ፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.