Fana: At a Speed of Life!

ሕግ የማስከበር ዘመቻው ውጤት እያመጣ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዞኑ እየተካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ውጤት እያመጣ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በወቅታዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን እንደተናገሩት ÷ የህግ ማስከበር ዘመቻው ከመካሄዱ አስቀድሞ ማኅበረሰቡን ያሳተፉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገዋል።

ከዕምነት ተቋማት አባቶች፣ ከሙያ ማኅበራት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተደረገው ውይይትና መግባባት ሕግ የማስከበር ዘመቻው ዉጤታማ እንዲሆን እንዳስቻለና ይህም ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለሚጠይቀው የ“ሕግ ይከበር “ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን መሆኑን ነው አስተዳዳሪው ያስረዱት፡፡

በእስካሁኑ ሕግ የማስከበር ሂደትም በዞኑ ሕግ በማይፈቅደው መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 422 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ነው የገለጹት።

ከነዚህም መካከል መለዮ የለበሱና እና በሕግ የሚፈለጉ ግለሰቦች ከነሕገ- ወጥ የጦር መሣሪያቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

በዚህም ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ሲያነሳ ከነበረው ቅሬታ እየተላቀቀ መምጣቱ ነው የተጠቆመው፡፡

የማኅበረሰቡን በሠላም ወጥቶ መግባት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲዉሉ የማድረግ እንቅስቃሴውን ዞኑ አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ አብዱ ፣ ሕዝቡ የተዛቡ መረጃዎችንና አሉባልታዎችን ከሚያሰራጩ የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እራሱን እንዲያርቅ እና ለሕግ መከበር ሂደቱ ያሳየውን ተባባሪነት እንዲያጠናክር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ ማኅበረሰቡ በእጁ የያዘውን የጦር መሣሪያ የማስመዝገብ ሂደቱ ውጤታማ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ፣ በቀጣይም ህዝቡ በእጁ የያዘውን ማንኛውንም የጦር መሣሪያ በማስመዝገብ ራሱን፥ አካባቢውንና ሀገሩን እንዲጠብቅ አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል።

በእሸቱ ወ/ሚካኤል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.