Fana: At a Speed of Life!

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ከዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ከዓለም የኢንተርኔት ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት አንድሪው ሱሊቫን ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም ተቋማቱ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በቅንጅት መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ኤጀንሲው የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እና መለኪያዎች ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖራቸው ከኢንተርኔት ሶሳይቲው ጋር በጋራ ለመስራት መስራቱን የኤጀንሲው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ መሰረት ኤጀንሲው በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የሚያከውናቸው ስራዎች ዓለም አቀፋዊነትን የተለባሱ እንዲሆኑ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እንደሚሰራ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በምርምር እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ላይ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተወያይተዋል።

ኤጀንሲ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የበይነ መረብ ደህንነት ንቃተ ህሊና ለማሳደግ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ የኢንተርኔት ሶሳይቲው አጋር ሆኖ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኢንተርኔት ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት አንድሪው ሱሊቫን ተቋሙ በመላው ዓለም የበይነ መረብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ደህንነቱን ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ጠቅሰው፥ ኤጄንሲው በዚህ ረገድ የሚያሰራቸውን ስራዎች ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የበይነ መረብ አገልግሎትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፥ ዘርፉ ይበልጥ ጠንካራ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

ከውይይቱ ጎን ለጎን ከዓለም አቀፍ ኢንተርኔት ሶሳይቲ በመጡ የቴክኒካል ባለሙያዎች ለኤጀንሲው ሠራተኞች በዓለም አቀፍ በይነ መረብ እና ደህንነት ዙሪያ ግንዛቤ ሊያዝባቸውና ጥንቃቄ ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

የኢንተርኔት ሶሳይቲ ከ29 አመት በፊት በኢንተርኔት ፈጣሪዎች አማካኝነት የተመሰረተ ሲሆን፥ በይነ መረብ በመላው ዓለም ተደራሽ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ተአማኒ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.