Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ  ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

የአስተዳደሩ ካቢኔ በቅድሚያ የፌደራል ሚስትሮች ምክር ቤት የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅት ለማቋቋም የወጣ ደንብ ላይ ተወያይቷል፡፡

በዚህም ለድርጅቱ ከተፈቀደ 150 ሚሊየን ካፒታል ብር 55 ሚሊየን በጥሬ ገንዘብና በአይነት  የተከፈለ ሲሆን÷ ደንቡ በአስተዳደሩ ድሬ ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና እንዲሆን ወስኗል፡፡

ካቢኔው  ከዚህ በፊት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የምድር ባቡር ድርጅት የአጠቃላይ  ሰራተኛ በድሬዳዋ የአየር ሁኔታ የሚያገለግል በመሆኑ ለሌሎች የአስተዳደሩ መንግስት ሰራተኞች ተፈቅዶ በስራ የዋለው የደመወዛቸው 20 በመቶ የበረሀ አበል ክፍያ ከግንቦት 1 ቀን ጀምሮ ደመወዝ ተጨማሮ እንዲከፈላቸው ወስኗል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የድርጅቱ የሰራተኞች ደመወዝ መሻሻል የሚገባው በመሆኑ የአስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ባለው የስራ ምዘና መሰረት የደመወዝ ማሻሻያውን ጥናት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጥንቶ ለካቤኔ ስብሰባ ውይይት  እንዲያቀርብ  ወስኗል፡፡

የኑሮ ውድነት ያስከተለውን ጫና አስመልክቶ ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ  ያቀረበው  የዳሰሳ  ጥናት የኑሮ ውድነቱን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታትና መፍትሄ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ መቅረቡ ተመላክቷል፡፡

በዚህ መሰረትም በቀጣይ ጥናቱ በዝርዝር የመፍትሄ ሀሳቦችን የሚጠቁም ሆኖ እንዲሻሻል ሀሳብና አስተያየት የተሰጠበት መሆኑን ከድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.