Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለካራማራ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለካራማራ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመልእክታቸው “ከዚያድ ባሬ መራሹ የሶማሊያ ወራሪ ኃይል ጋር በነበረን ተጋድሎ ወሳኝ ድል ላስመዘገብንበት የካራማራ ድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት

የ1967ቱ የሶማሊያ ወረራ ሀገራችን ከአብዮት ፍንዳታው ጭጋግ ባልወጣችበትና የእርስ በርስ ግጭት ላይ በነበረችበት ጊዜ የተከሠተ ነው። ኢትዮጵያን የወረሩ አብዛኞቹ ኃይሎች እንደሚሠሩት ስሕተት ዚያድ ባሬም ተሳሳተ።

ሀገር የደከመች መስሎት ኢትዮጵያን የማሸነፊያ ጊዜ የደረሰለት መሰለው፤ በዚህ የተሳሳተ ስሌት ተመርቶ ወረራውን ፈጸመ። በመጀመሪያ አካባቢ እንዳሰበውም የጎላ መከላከል ሳይገጥመው ሰፊ የሀገራችንን መሬት ማካለል ችሎ ነበር።

ነገር ግን ኢትዮጵያውያን እንደፍግ ተኝተው እንደ እቶን በተነሡ ጊዜ ምን እንደሚያደርጉ በዚህ ወረራ ጊዜ ታየ።

በአጭር ጊዜ “የእናት ሀገር ጥሪ” የተሰባሰቡ፣ በቂ የሥልጠናም ሆነ የዝግጅት ሁኔታ ያልነበራቸው፣ ነገር ግን ከየትም የማይበደሩት የሀገር ፍቅርና የማሸነፍ ወኔ ያላቸው ውድ ኢትዮጵያውያን ወረራውን በስኬት መቀልበስ ቻሉ።

መንግሥታትን በሀገር ውስጥ ክዋኔያቸው በአንድም በሌላም ልንመዝናቸው እንችላለን፤ ነገር ግን የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የሚከፈሉ መሥዋዕትነቶች በየትኛውም ዘመን ቢፈጸሙ የሀገራችን ታሪካዊ ኩራት ናቸው።

የደርግ መንግሥትም በአጭር ጊዜ ጥሪ አቅርቦ፣ አሠልጥኖና አደራጅቶ የሀገርን ክብር ለማስመለስ ያደረገው ተጋድሎና ያስመዘገው ድል የሁላችንም የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነትና ለሀገር የመሥዋዕትነት የመክፈል ታሪካችን አካል ነው።

ሁሌም በውስጣችን ክፍተት ሲኖር የውጭ ጠላት እንጋብዛለን፤ ስንጠናከር ግን የታፈርንና የተከበርን እንሆናለን።

በዚህ አጋጣሚ ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሠልፈው የተዋጉትንና ውድ ሕይወታቸውን የሠዉትን የኩባ እና የየመን ወታደሮችን ውለታ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል።

ክብር ሀገርን ለማቆየት ራሳቸውን መሥዋዕት ላደረጉ ኢትዮጵያውያን!

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.