Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ ሠራዊት የዩክሬንን ስትራቴጂያዊ ከተማ ሊማንን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ጦር ስትራቴጂያዊ ፋይዳዋ ክፍተኛ ነው የተባለችውንና ምስራቃዊቷን የዩክሬን ከተማ ሊማንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን አረጋገጠ፡፡

የሩሰያ ጦር በዩክሬን ምሥራቃዊ ክፍል ዶንባስ ክልል የሚያደርገውን የማጥቃት ዘመቻ አጠናክሮ በመቀጠል የሊማን ከተማ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የሩሲያ ጦር ወደ ስሎቪንስክ የሚያደረገውን ግስጋሴ የዩክሬን ተከላካይ ኃይሎች እንደገቱት የሚያመላክት መረጃ በዩክሬን በኩል ወጥቶ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡

በዩክሬን ሉሃንስክ ግዛት ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች መሰማራታቸውን የዩክሬን ምሥራቃዊ ክልል አስተዳዳሪ መናገራቸውን በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

የዩክሬን ጦር በመከላከል እና የሩሲያ ኃይሎች ደግሞ የሊማን ከተማ ለመቆጣጠር ለብዙ ቀናት ብርቱ ውጊያ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም የቲአርቲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የሩስያ ጦር የአንዱስትሪ ተቋማት ማዕከል በሆነው በዶንባስ ክልል የሚያደርፈገው ውጊያ
እየከፋ በመምጣቱ ምዕራባውያን አገራት የጦር መሳሪያ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ ሃይፐርሶኒክ ዚርኮን ክሪዝ የተባለ ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ ማስወንጨፏን የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል።

የሚሳኤል ሙከራው የተካሄደው በአርክቲክ ባሬንትስ ባህር ውስጥ ሲሆን፥ በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘውን ዒላማ በተሳካ ሁኔታ መምታቱን የሚኒስቴሩ መግለጫ ጠቁሟል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ተምዘግዝገው ዒላማቸውን የመምታት አቅም ያላቸው አዳዲስ ሚሳኤሎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ በውጊያ ግዳጅ ላይ እንደሚሰማሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ከሳምነት በፊት የሩሲያ ወታደሮች ከኪየቭ ቀጥላ ትልቋን ሁለተኛ ከተማ፥ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዋ ከፍተኛ የሆነችውንና የዩክሬን የወደብ ከተማ ማሪዮፖልን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸው ይተወሳል።

ከተማዋን ለመቆጣጠርም ለአንድ ወር ያህል ሁለቱ ወገኖች ህይወትም ንብረትም ያወደመ ፍልሚያ ማካሄዳቸው ተመላክቷል ፡፡
በተለይም በማሪዮፖል ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አዞቭስታል የተሰኘው የብረት ፋብሪካ ውስጥ መሽገው ሲዋጉ የቆዩ 531 የዩክሬን የመጨረሻ ወታደሮች ለሩሲያ እጅ ለመስጠት ተገድደዋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳን ቮሎድሚር ዘለንስኪ በአዞቭስታል የብረት ፋብሪካ የሩሲያን ጦር ሲመክቱ የነበሩ የአገራቸው ወታደሮች ስፍራውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበርም ሞስኮ ታይምስ በዘገባው ማስፈሩ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.