Fana: At a Speed of Life!

“የድርቁ አደጋ የሰው ህይወት ሳይነጥቅ ምላሽ እንደተሰጠ ሁሉ ለዋጋ ንረቱም ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው”- አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የድርቁ አደጋ የሰው ህይወት ሳይነጥቅ ምላሽ እንደተሰጠ ሁሉ ለዋጋ ንረቱም ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው” ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት በክልሉ እየታየ ያለውን የዋጋ ግሽበት በሀገራችን እና በዓለም እያስከተለ ያለውን የዋጋ ንረት ብቻውን ሊፈታው አይችልም ብለዋል።

ነገር ግን የክልሉ መንግስት ለድርቁ አደጋ የሰው ህይወት መጥፋት ሳያስከትል ምላሽ እንደሰጠው ሁሉ፣ መንስኤው ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ የሆነውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የተለያዩ ስትራቴጂዎችን እና እቅዶችን አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መግለፃቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለፃ፥ የክልሉ መንግሥት ከወራት በፊት ከወሰዳቸው ስትራቴጂዎች መካከል ህገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድን መቆጣጠር፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ድጋፍ ማድረግ፣ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ሲሆኑ፥ እነዚህ በጅምር ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች በመሆናቸው መጠናከር እና በፍጥነት መተግበር አለባቸው ነው ያሉት ።

በተጨማሪም መንግሥት የአገር ውስጥ በጀትና ተቋማዊ የገንዘብ ድጋፍን ተጠቅሞ ምን ማድረግ እንደሚችል ትኩረት አድርጎ እየሰራበት መሆኑንም ነው ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ የጠቆሙት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.