Fana: At a Speed of Life!

ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል የተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ምንም ዓይነት ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖ የለበትም – ዶክተር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተጀመረው የሕግ ማስከበር ሥራ ምንም ዓይነት ውጫዊና ውስጣዊ ጫና የሌለውና ዋነኛ ግቡም የሕዝብን ሠላምና ደኅንነት ማስከበር እንደሆነ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

ሠላም የሁሉም መሠረት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ፣ ያለ ሰላም ኢኮኖሚያዊ ልማቶችንና መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ ማከናወን እንደማይቻል ተናግረዋል።

ሠላም ከሌለ ዜጎች የኢኮኖሚ ፍላጎታቸውን በአቅማቸው ልክ ተረባርበውና ተቀናጅተው መሥራትም ሆነ ማሟላት አይችሉምም ብለዋል።

ሕገ-ወጥነትንና ሥርዓት አልበኝነትን መቆጣጠር ከተቻለ የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ማከናወን እንደሚቻል ለአርሶ አደሮች ርክክብ የተደረጉትን ትራክተሮች እንደማሳያ በመጥቀስ አስገንዝበዋል።

ዶክተር ይልቃል ÷ በክልሉ የተጀመረው የህግ ማስከበር ሥራ ሠላም እና ደኅንነትን በዘላቂነት ከማረጋገጥ ውጭ የተለየ ሤራ እንደሌለውም ተናግረዋል።

ሁሉም ይህን ተገንዝቦ ጥረቱን ከመንግስት የፀጥታ መዋቅር ጎን ሆኖ እንዲደግፍ አሳስበዋል።

“ለሁሉም ነገር አስተማማኝ ሠላም፣ደኅንነትና ህግ የተከበረበት ሥርዓት ማስፈን በእጅጉ ያስፈልጋል” ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ናቸው።

አቶ ግርማ የሺጥላ ÷ ውስጣዊ አንድነትን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ማጠናከርና በዋናነት ውጫዊ ጠላታችን ላይ ማተኮር እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.