Fana: At a Speed of Life!

የተመድ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ህብረት ኢትዮጵያን እንዲደግፍ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ህብረት ኢትዮጵያን እንዲደግፍ ተጠየቀ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ጀኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ህብረት ቢሮ ተገኝተው ከህብረቱ ዋና ጸሀፊ ሆሊን ዣዎ ጋር ተወያይተዋል።

ቀደም ብሎ በተወሰነው መሠረት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ቴሌኮም ልማት ጉባኤን በሰኔ ወር አዲስ አበባ ላይ እንድታዘጋጅ እድሉ የተሰጣት ሲሆን፥ ሚኒስቴሩ የወሰደውን ሀገራዊ ሀላፊነት ተከትሎ በርካታ ዝግጅቶችን ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል።

ሆኖም ከወራቶች ቀደም ብሎ በነበረው ሀገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት ስለኢትዮጵያ ሲያስተጋቡት በነበረው የተሳሳተ ምስልና ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም አንዳንድ ሀገራት በወቅቱ በያዙት አቋም ምክንያት ህብረቱ ለኢትዮጵያ የተሰጠውን እድል አንስቶ ለሌላ ሀገር አስተላልፏል።

ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ሀገር የተሰጠው እድል ወደ ሩዋንዳ የተላለፈ ሲሆን ፥ ሩዋንዳም ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ጉባኤውን ታስተናግዳለች።

አጠቃላይ ሂደቱን አስመልክቶ ሚኒስትሩ ፥ ኢትዮጵያ የተሰጣትን እድል በስኬት ለማካሄድ በርካታ ዝግጅቶች ስታደርግ የቆየች መሆኗን ጠቅሰው ፥ በሂደቱም ከፍተኛ ሀገራዊ ጊዜና ሀብት ያወጣች መሆኑን በማስታወስ በተወሰደው በውሳኔው ኢትዮጵያ እጅጉን ቅር መሰኘቷን ገልጸዋል።

ሆኖም ያለፈውን እንደመማሪያ ወስዶ ህብረቱ ኢትዮጵያን መካስ በሚያስችለው ሁኔታ ለወደፊት ቅድሚያ ሰጥቶ ጉባኤወችን አዲስ አበባ ላይ እንዲያደርግና በተጨማሪም የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎችን ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የህብረቱ ዋና ጸሀፊም ለሆነው ሁሉ ይቅርታ ጠይቀው የተሰማቸውን ስሜት በመግለጽ የሚኒስትሩን ጥያቄወች ተቀብለው ለወደፊት ህብረቱ ኢትዮጵያን እንዲክስና እንዲደግፍ አበክረው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ሩዋንዳ የተሳካ ጉባኤ እንድታካሂድ ሚኒስትሩ በዚህ አጋጣሚ መልካም እድል መመኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.