Fana: At a Speed of Life!

የጃፓን ኢምፓክ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ የሚያስገባውን የጽጌረዳ አበባ በአምስት እጥፍ ሊያሳድግ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓን ኢምፓክ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ የሚያስገባውን የጽጌረዳ አበባ በአምስት እጥፍ ሊያሳድግ ነው፡፡

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፥ የኢምፓክ ኮርፖሬሽን ሊቀመንበር እና ፕሬዚዳንት ሄኪሮ ሞሪሽጌ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሮዝ አበባ ንግድ ላይ መክረዋል።

የኢምፓክ ኮርፖሬሽን ሊቀመንበር እና ፕሬዚዳንት ሄኪሮ ሞሪሽጌ ለአምባሳደር ተፈራ ገለጻ ሲያደርጉ እንዳነሱት ፥ ኢምፓክ ኮርፖሬሽን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጽጌረዳ አበባ አብቃይ እና ላኪዎች በዓመት 2 ሚሊየን የሮዝ አበባ ዘንግ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል።

ከዚህ ባለፈም ኮርፖሬሽኑ ፥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባውን ዓመታዊ የጽጌረዳ አበባ መጠን በአምስት እጥፍ ለማሳደግ አቅዷል።

በተጨማሪም ኢምፓክ ኮርፖሬሽን በጃፓን ተጠቃሚዎች የኢትዮጵያን የጽጌረዳ አበባ ፍላጎት ለመፍጠር እያደረገ ስላለው ጥረት ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገዋል።

ለዚህም ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን የሮዝ አበባን ለአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች፣ ለአበባ ተመራማሪዎች እና የአበባ መሸጫ ሱፐርማርኬቶችን በጃፓን ለማስተዋወቅ በማሰብ በጥቅምት እና ህዳር 2022 እና በየካቲት 2023 የሮዝ አበባ ኤግዚቢሽን ለማድረግ እንዳቀደም ነው የተገለጸው።

አምባሳደር ተፈራ በበኩላቸው ፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ቶኪዮ የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ መጀመሩን ተከትሎ ኢምፓክ ኮርፖሬሽን የጽጌረዳ አበባ ላይ ያደረገውን ንግድ አድንቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባውን የአበባ ምርት መጠን በአምስት እጥፍ ለማሳደግ ያቀደው መሆኑንም አመስግነዋል።

አያይዘውም ኢምፓክ ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባውን የአበባ ምርት መጠን ከማስፋት ባለፈ በአበባ ልማት ኢንቨስት እንዲያደርግ አበረታተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ፥ አምባሳደር ተፈራ በሳይታማ ከተማ የሚገኘውን የአበባ ማቀነባበሪያና ማከፋፈያ ፋብሪካን እንዲጎበኙና በዚህ ዓመት መጨረሻና በ2023 መጀመሪያ ላይ በተዘጋጀው የአበባ ኤግዚቢሽን ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል።

አምባሳደሩ ግብዣውን ተቀብለው ፥ ኤምባሲው ከኢምፓክ ኮርፖሬሽን ጋር የሚያደርገውን ትብብርና ለሆርቲካልቸር ኤግዚቢሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.