Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፍ ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው – የተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለትግራይ ክልል ሕዝብ እየቀረበ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ መልካም የሚባል መሆኑን እና የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፉ ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሀና ቴቴክ ተናገሩ፡፡
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ከተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሀና ቴቴክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ በወቅታዊ የአገራችን የዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራዎች፣ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተደረገ ስለሚገኘው ሰብዓዊ ድጋፍና በሌሎች የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ለትግራይ ክልል ሕዝብ እየቀረበ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ መልካም የሚባል መሆኑን የገለፁት ልዩ መልዕክተኛዋ÷ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፉ ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
በሌሎች ክልሎችም በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገውን ሰብዓዊ ድጋፍ በማገዝ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት በመደገፍና በቀጣይ የሚደረገውን አካታች ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ ለማድረግና ሀገራዊ ምክክሩ በሰላም ግንባታው ላይ የሚኖረውን አዎንታዊ ተፅኖ በመደገፍ ከኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ጎን እንደሚቆሙም ልዩ መልዕክተኛዋ መናገራቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.