Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በአንድ ጀንበር 250 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ሀምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 250 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ተገልጿል፡፡
 
ክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶችን ለመትከል ዝግጅት እያደረገ መሆኑም ነው የተመላከተው፡፡
 
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥እስካሁን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኝ ዝግጁ ተደርጓል ብለዋል።
 
በክልሉ እስካሁን 25 ሚሊየን ጉድጓድ ተዘጋጅቷል ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊዋ÷ ሀምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም 250 ሚሊየን ችግኝ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በአንድ ጀንበር ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
 
ባለፈው ዓመት በክልሉ ከተተከለው 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኝ ውሰጥ 84 በመቶው መፅደቁን ነው የቢሮው መረጃ የሚጠቁመው።
 
በሌላ በኩል የአፋር ክልል እንስሳት፣እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡስማን መሀመድ አህመድ በበኩላቸው ÷ ባለፈው ዓመት ከተተከለው 4 ሚሊየን ችግኝ የፀደው 35 በመቶው ብቻ ነው ብለዋል፡፡
 
በክልሉ የነበረው ጦርነት፣ የዝናብ እጥረት እና ሌሎች ምክንያቶችን ለፅድቀት መጠኑ መቀነስ የጠቀሱ ሲሆን÷ ይህን በሚያካከስ መልኩ ዘንድሮ ከ 14 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል።
 
ከዚህ ውስጥም 4 ሚሊየን ያህል ችግኞች ከምግብ ዋስትና ጋር የተያያዙ እንደሚሆኑ ነው ኃላፊው ያነሱት፡፡
 
ሁለቱም ክልሎች በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የምግብ ዋስትና ጋር የተያያዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ላይ ትኩረት እንደሚደርጉ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።
 
በዙፋን ካሳሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.