Fana: At a Speed of Life!

በሰበታ በ100 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተገነባው የኮካ ኮላ ማምረቻ ፋብሪካ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ በ100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በ“ኮካ-ኮላ መጠጦች አፍሪካ ኢትዮጵያ” ኩባንያ የተገነባው የኮካኮላ ምርት ማምረቻ ፋብሪካ ተመረቀ፡፡

ፋብሪካው የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የተመረቀው።

ኩባንያው ላለፉት ስድስት አስርት-ዓመታት በኢትዮጵያ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን÷ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ እድል መፍጠሩም ተመላክቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ድርጅቱ ባለፉት 62 ዓመታት በኢንዱስትሪ ዘርፍ የማይተካ ሚና አበርክቷል ብለዋል፡፡

መንግስት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ዘርፉን ለማጎልበት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ኩባንያው እያከናወናቸው ላሉ የልማት ስራዎች የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኮካኮላ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሬል ዊልሰን÷ ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ በመመደብ የተለያዩ የማስፋፋፊያ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተመረቀው ፕሮጀክትም የዚሁ አካል መሆኑን አመላክተዋል።

በሰበታ ከተማ የተመረቀው ፋብሪካ ኮካኮላ ምርት ከሚያመርትባቸው ፋብሪካዎች 5ኛው ቅርንጫፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዛሬው ዕለት የተመረቀው የኮካ ኮላ ማምረቻ ፋብሪካ ኮካ-ኮላ ቢቭሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያን በዓመት ከ100 ሚሊየን በላይ እሽግ ለስላሳ ለማምረት ያስችለዋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የማምረቻ ግብዓቶችን እንደ የፕላስቲክ ጠርሙስ እና ክዳን እንዲሁም ሌሎች የምርት ግብአቶችን በማምረት ከውጪ ወደ ሀገሪቷ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ እንደሚኒት ሜዲ ጁስ የመሳሰሉ አዳዲስ ምርቶችን ሀገር ውስጥ በማምረት ጠቅላላ ምርት ለመጨመር እንደሚረዳም ነው የተገለጸው፡፡

 

ለተጨማሪ መረጃ ቪዲዮውን ይመልከቱ ፡-

 

የሚመረቱት የግብአት ምርቶቹ የሲ ሲ ቢ ኤን ፍላጎት ከማሳካት በተጨማሪ ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጨ ምንዛሬን ሀገሪቷ እንድታገኝ እና በዘርፉ ያለውን የምርት እጥረት ለመፍታት ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብም ፋብሪካው እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡

በሀብታሙ ተ/ስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.