Fana: At a Speed of Life!

ከልማት አጋሮች የሚገኘውን ሀብት በግጭት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ለማዋል ግልጽ አሰራር እንደሚተገበር ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ከልማት አጋሮች የሚገኘውን የውጭ ሀብት በግጭት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ለሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ለማዋል አሳታፊ የሆነ አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦቶች ላይ በየመንፈቅ ዓመት የሚደረገው የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው÷ በመሰረታዊ አገልግሎቶች ተግባራዊ በተደረጉ ፕሮግራሞች አቅርቦትን በማሻሻልና ባልተማከለ አስተዳደር ተጠያቂነትን በማስፈን ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢኖሩም ሀገሪቱ ካሳለፈችው ፈታኝ ሁኔታ አንጻር ዜጎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ባለድረሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅናቸው አመልክተዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታዋ ባለፈው የምክክር መድረክ ላይ የተነሱ ችግሮች ላይ በመስራቱ ውጤት እንደተገኘ ተናገረው፥ በቀጣይ የገንዘብ ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የአፈጻጸም ስትራቴጂ በመንደፍ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የማህበራዊ ተጠያቂነት፣ የፋይናንስ ገልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሁም የቅሬታ አፈታት ስልት ግንኙነት መመሪያንና ሌሎችንም ጅምር ስራዎች ከግብ ለማድረስ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የመሰረታዊ አገልግሎትን በፍትሀዊነት በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ ዜጎች ለማዳረስ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው አመላክተዋል።

ከልማት አጋሮች የሚገኘውን የውጭ ሀብት በግጭት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ለሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ለማዋል አሳታፊ የሆነ አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ባለፉት ዓመታት በፌደራል መንግስት፣ በልማት አጋሮች፣ በክልሎች፣ በወረዳዎች ትምህርትን፣ ጤናን፣ የገጠር መንገድን፣ ግብርናንና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም የአካባቢንና የግል ንፅህናን ለማስፋፋትና ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰጥ ለማስቻል ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ የልማት ፕሮግራም ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.