Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ተጎጂዎች እኩል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ተጎጂዎች እኩል ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቁ።

አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ቴቴ ጋር በሀገራዊ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ገለፃ አድርገዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት በቀጠናው ሰላም እና ልማት ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር ልዩ መልዕክተኛዋ እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እና የፈጸማቸውን ተግባራት ለልዩ መልክተኛዋ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል መተማመንን ለማጠናከርና አስተማማኝ ሰላምን ለመፍጠር መንግስት ሁሉን አቀፍ ስራዎችን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ አደጋዎች ተጎጂ ለሆኑ እና በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ህዝቦች እርዳታን ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ደመቀ ፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚገኙ ተጎጂዎች እኩል ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ቴቴ ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት መስራች መሆኗን አስታውሰው፥ በርካታ ዓመታት ያስቆጠረውን ትብብር በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ መንግስት እየወሰዳቸው ላሉ የሰላም ጥረቶችም አድናቆታቸውን ገልፀዋል ።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋጥ በትኩረት እንደሚሰሩ የተናገሩት መልዕክተኛዋ ፥ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ጥረታቸውን እንደሚደግፍ እምነት እንዳላቸው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.