Fana: At a Speed of Life!

በጅግጅጋ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማት ለማሳደግ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሻፊ አህመድ ፥ የክልሉ መንግስት ከለውጡ ወዲህ ባለፉት ሦስት ዓመታት በከተማው የነበረውን ዝቅተኛ የመንገድ ተደራሽነት ለማሻሻልና ህዝቡን ዘመናዊና ጥራት ያለው የመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ አምስት የአስፋልት መንገዶችን አስገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 7 ኪሎ ሜትር የሚደርስ አራት የጠጠር መንገዶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ ፥ በከተማው እየተካሄዱ ከሚገኙ መንገዶች ውስጥ ሶስቱ በዓለም ባንክ በሚደገፈው የከተሞች ተቋማዊና የመሠረተ ልማት ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና አንዱ መንገድ ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ አቅም እየተገነቡ ያሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ስራ አስኪያጁ በከተማው በግንባታ ላይ የሚገኙት የአስፋልት መንገዶች የአየር ሃይል አካባቢ፣ ከዋናው መንገድ ወደ ጀላባ የሚገነባው የጠጠር መንገድ ፣ የታይዋንና የነርሲንግ አካባቢ መንገዶች መሆናቸውን ጠቁመው ፥ መንገዶቹን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢንጂነር ሻፊ አህመድ ፥ በከተማው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አማካኝነት የሚገነባው ሰባት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መንገድ 30 ባይፓስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

የጅግጅጋ የጠጠር መንገድ ግንባታ አማካሪ መሀንዲስ ኢንጂነር ቴድሮስ አምሳሉ በበኩላቸው ፥ በጅግጅጋ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኙ የጠጠር መንገዶች ግንባታ 80 ከመቶ መድረሱን ጠቁመው ፥ በቀጣይ መንገዶቹን ወደ አስፋልት ደረጃ ለማሳደግ እቅድ መያዙን መናገራቸውን ከክልሉ መገናኛ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.