Fana: At a Speed of Life!

ከ129 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ129 ሚሊየን 152 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል ነው 102 ነጥብ 8 ሚሊየን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 26 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ አማካኝነት የተያዙት፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ አዲስ አበባ ኤር ፖርት እና አዲስ አበባ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆኑ÷ በቅደም ተከተላቸው 37 ነጥብ 9 ሚሊየን ፣ 16 ነጥብ 7 ሚሊየን እና 14 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዛቸው ተመላክቷል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል÷አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.