Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ ከትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላምን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላምን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የትምህር ጥራትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ እና በተያየዥ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ትምህርት መሆኑን ገልጸው÷ለማሳያነትም ከሃገሪቱ ዓመታዊ በጀት 20 በመቶው ለዘርፉ እንደሚመድብ ጠቁመዋል።
ትምህርትን በማስፋፋት እና ተደራሽነትን በማሳደግ ብዙ ውጤት መገኘቱን የጠቀሱት አቶ ደመቀ ÷ አሁን ላይም በጥራት ላይ ያለውን ጉድለት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለያዘችው የትምህርት ጥራትን የማሳደግ እቅድ በዘርፉ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ከተቋማቱ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክርም ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም በበኩላቸው ÷ የትምህርት ትብብር ድርጅት የደቡብ ደቡብ ትብብርን ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ዋና ጸሃፊው ኢትዮጵያ በድርጅቱ ውስጥ ያላት ሚና ከፍ እንዲል ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው÷ የድርጅቱን ዋና ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ላይ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል።
አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እና የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና መስሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ለማድረግ መፈለጉን ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም ገልፀዋል።
ጥያቄው በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ታይቶ ምላሽ እንደሚሰጠው በውይይቱ ላይ መመላከቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የትምህርት ትብብር ድርጅት በፈረንጆቹ 2020 የተመሰረተ 27 የአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ ፣ እስያ ፣ የላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን አገራት በአባልነት ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ድርጅቱ የሰብዓዊ ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ልማትን ለማምጣት የተመጣጠነ የትምህርት እድገት ላይ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለመስራት የተቋቋመ ነው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.