Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲያጋጥም ተገቢው ክትትል እና ማጣራት ተደርጎ የሕግ ተጠያቂነት እየሰፈነ ነው- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ከአሜሪካ ኮንግረስ አባል ትሬንት ኬሊ ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና አሜሪካ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እና በተለያዩ ጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
 
አቶ ታገሰ ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እርዳታ ለማዳረስ ያላሰለሰ ጥረት እደረገች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
 
በተለያዩ መንስኤዎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው መንግስት በያዘው በጎ አቋም በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ቢሆን እርዳታ የማዳረሱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።
 
ከዚህ ባለፈም ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ተገቢው ክትትል እና ማጣራት ተደርጎ የሕግ ተጠያቂነት እየሰፈነ መሆኑን አፈ ጉባኤው አብራርተዋል።
 
የሕግ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ በመንግስት በኩል ባለው ተነሳሽነት ሕግ የማስከበሩ ሥራ ትኩረት እንዳልተነፈገው ገልጸዋል።
 
ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላሟን እና አንድነቷን በተሻለ ሁኔታ ጠብቃ ለማቆየትም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቅርቡ መመሥረቱንም አስረድተዋል።
 
ትሬንት ኬሊ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸው መልካም ስራዎች ሁሉ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
 
ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እና ሕግጋት በሙሉ መከበራቸውን መንግስት እንደሚያረጋግጥ ያላቸውን ዕምነት መግለጻቸውንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.