Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ-ሳይበር ታለንት ማዕከል ለሌሎች አፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው – ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም

አዲስ አበባ፡ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና ጸሃፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና መስሪያ ቤትን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ ሀገር በቀል የሳይበር ቴክኖሎጂ ውጤቶችንና በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች የማልማት ሥራን ጎበኙ ሲሆን ፥ ስራዎቹና ተሞክሮዎቹ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለው ትምህርትን በማቅረብ፣ በሳይበር ሉአላዊነት፣ በዲጂታላይዜሽንና በታለንት ልማት ዙሪያ በአፍሪካ ደረጃ እየተሰራ ያለውን ሥራ ለመመልከት የሚያስችላቸውን ጉብኝት አካሂደዋል፡፡

አፍሪካውያን በዜጎቻቸው የሚለሙ አገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመጠቀም የዲጂታል ሉዓላዊነታቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ያሉት ሼክ መንሱር ፥ ከዚህ አኳያ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የለሙና እየለሙ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ለአህጉሩም ጭምር ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡

ኢመደአ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች በማልማት ረገድ የጀመረው ሥራ ከሳይበር ደህንነት ውጪ በሌሎች ዘርፎች ላይም ለተሰማሩ ተቋማት ምሳሌ እንደሚሆን የገለጹት ሼክ መንሱር ፥ በሁሉም ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች እንዳሉና እነዚህን ማልማት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም በፈረንጆቹ 2020 የተቋቋመ ሲሆን ፥ ዋና ዓላማውም በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ያሉ የተቋሙን አባል አገራት የልሂቃን፣ የሃብትና መሰል አቅሞችን በማስተባበር ጥራት ያለውና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አካታች ትምህርት ለሁሉም በማቅረብ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው፡፡

ዋና ጸሃፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ማነጋገራቸውም ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.