Fana: At a Speed of Life!

አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ያደረጉ ችግሮች እንዲፈቱ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ የሚያደርጉ ችግሮች እንዲፈቱ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አሳሰቡ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግሮች ለመፍታትና ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ያለመ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላም÷ አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ከባለሃብቶቹ ጋር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ፣ የአገር ውስጥ ግብዓትን ተጠቅመው የሚያመርቱ አገር በቀል ፋብሪካዎችን እና ገቢ ምርቶችን ለመተካት የሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎች ያሉበትን ሁኔታ እና ባሉባቸው ችግሮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በዚህም ዘርፉ ከወትሮው በተለየ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ በመሆኑ የተሻለ ለውጥ መምጣቱ የተመላከተ ሲሆን÷የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርም በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የኃይል መቆራረጥ፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የስራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት እና በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ሙሉ በሙሉ የማምረት አቅማቸውን ተጠቅመው እንዳያመርቱ አንዳደረጋቸውም ተገልጿል፡፡
አቶ መላኩ አለበል በውይይቱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ÷ በክልል፣ በከተማ አስተዳደሮች እና በፌደራል ደረጃ የሚፈቱ ችግሮች መለየታቸውን ገልጸው÷ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.