Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ አመራሮች በተመደቡበት ቦታ ማህበረሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል አለባቸው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በተመደቡበት ቦታ ማህበረሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ፡፡
“አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ – አዲስ ሀገራዊ እምርታ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ ሀሳብ እና የቀጣይ የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ብልፅግና ብዝሃነትን የተቀበለ፣ ብዝሃነትን የሚያከብርና በአግባቡ እውቅና ሰጥቶ የሚንከባከብ፣ አንድነታችንን ደግሞ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
የብልፅግና አመራር ሰላምን በማንገብ ሀገራዊ ብልፅግና እውን እንዲሆን በማድረግ ረገድ ያለው ሚና እና አስተዋጽኦ ከፍ ያለ በመሆኑ አመራሩ በታማኝነትና በቅንነት ስራዎችን መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
በጋራ በመቆም፣ ተጠያቂነትን በማስፈንና በአገልግሎት ዘርፉ ውጤታማ ተግባራትን በመከወን ለሕዝቡ በምርጫ ወቅት የተገባው ቃል ሊፈጸም እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ÷ ለአመራሩ የተሰጠው ስልጠና የአመለካከት ክፍተቶችን የሞላ እና የአመራሩን ችግሮች በመለየት የመፍታት አቅምን ያዳበረ ነው ብለዋል፡፡
አመራሩ በቀሪ የተግባር ምዕራፎች የተቋም ግንባታን በማጠናከር ያሉትን ስራዎች በጥራትና በውጤት መተግበርና መፈጸም እንደሚገባውም አቶ መለሰ አሳስበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.