Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል ፖሊስ ለ55 ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለ55 ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጥቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመለሽ ገ/ሚካኤል፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች፣ የፌደራልና የሁሉም ክልሎች ፖሊስ ኮሚሽነሮችና እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የማዕረግ እድገቱን ያገኙት ከፍተኛ መኮንኖች፥ ባሳዩት የተሻለ የአመራር ብቃት እና በሥራ አፈጻጸማቸው በሰራዊቱ የተመሰከረላቸው በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገርን ማገልገል ወርቃማ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው፥ እድልን ሳያባክኑ መጠቀም ጥበብና አስተውሎት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በየትኛውም አቅጣጫ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን ጥቃት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመመከት አሁንም የተጠናከረ ኃላፊነት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው፥ ፖሊስ የተሰጠውን ኃላፊነት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተሰጠው የማዕረግ እድገትም ከኮማንደርነት ወደ ረዳት ኮሚሽነርነት 43 እንዲሁም ከረዳት ኮሚሽነርነት ወደ ምክትል ኮሚሽነርነት 12 አመራሮች ማደጋቸውን ገልጸው፥ በአጠቃላይ 55 አመራሮች የማዕረግ ዕድገት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

እድገቱን ያገኙት አመራሮችም፥ ባላቸው ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት፣ በያዙት ማዕረግ ከ4 ዓመት በላይ የቆዩ፣ በመምሪያ ኃላፊነትና ከዚያ በላይ የኃላፊነት ደረጃ ያላቸው እንዲሁም በሠራዊቱ ዘንድ ባላቸው መልካም ፖሊሳዊ ሰብዕና መመዘኛዎች ነው ብለዋል፡፡

ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተሞች ፖሊስ እንዲሁም ከአፋር እና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ፖሊስ ኮሚሽን ለተውጣጡ ስትራቴጂክ አመራሮች ነው የማዕረግ ዕድገቱ የተሰጠው፡፡
በአዳነች አበበ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.