Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በምግብ  ራሷን ለመቻል  ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው – የአፍሪካ ልማት ባንክ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 26፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በምግብ  ራሷን ለመቻል  ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ሲሉ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አድሲና  ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ከቡድን 7 አገራት የልማት ሚኒስትሮች ጋር ባደረጉት ውይይት እንዳስረዱት ከሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ አፍሪካ ከ30 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ አቅርቦት እጥረት አጋጥሟታል ብለዋል፡፡

ጦርነቱ በተለይ ከሁለቱም ሀገራት በሚገቡት የስንዴ፣ በቆሎ እና አኩሪ አተር ምርቶች ወደ አህጉሪቷ በብዛት እንዳይገቡ ማድረጉን ነው ያስረዱት።

የምግብ ቀውስ እየተከሰተ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን ለመቻል ወሳኝ እርምጃዎችን የወሰደች አፍሪካዊት አገር ናት ብለዋል።

ሀገሪቱ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በግብርና ቴክኖሎጅዎች ዙሪያ በትብብር በመስራቷ ምርታማነትን ማሳደጓን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ከ61 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ሙቀትን መቋቋም የሚችል የስንዴ ዘር ማቅረብ መቻሉንም አስግንዝበዋል፡፡

በቀረበው የተሸሻለ ዝርያም ኢትዮጵያ የምታለማውን የስንዴ ምርት መጠን አስፍታለች ያሉት ሃለፊው፥ በ2018 የነበረው 50 ሺህ ሄክታር የስንዴ ምርት ሽፋን በ2021 ወደ 167 ሺህ ሄክታር፣ በ2022 ደግሞ ወደ 400 ሺህ ሄክታር ማደጉን አመላክተዋል፡፡

ሃላፊው በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በ650 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ እያመረተች እንደምትገኝ እና በሚቀጥለው አመት ደግሞ በ2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማምረት እቅድ መያዟን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሀገሪቱ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ቶን ምርት የሰበሰበች ሲሆን፥ በሚቀጥለው አመት ወደ ኬንያ እና ጅቡቲ መላክ ለመጀመር ማቀዷንም ተረድቻለሁ ሲሉ ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.