Fana: At a Speed of Life!

በምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ቀሪ ስራዎች ዙሪያ ከአገራቱ አምባሳደሮች ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ላይ ከሚሳተፉ አገራት አምባሳደሮች ጋር በፌስቲቫሉ ዝግጅት ዙሪያ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት ተደረገ፡፡

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተባባሪ አካላት ከሰኔ 7 እስከ 12 ቀን 2014 ዓ.ም “ጥበባትና ባህል ለቀጠናዊ ትስስር! “ በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ፌስቲቫሉ ይካሄዳል፡፡

በውይይቱም የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ፥ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫሉ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለመፍጠር እና የባህል ዲፕሎማሲን ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ፌስቲቫሉ በዓውደ ጥናት፣ በዐውደ ርዕይና በልዩ ልዩ ባህላዊ ሁነቶች እንደሚከናወን ነው የገለጹት፡፡

ሚኒስትሩ አገራቱ ሁኑቱን አስመልክቶ በተለይም ተሳታፊ ልዑካን ቡድኖች እንዲገኙ ከማድረግ አንፃር ስራው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማወቅ በቀጣይ ለምናካሂደው ሁነት ወሳኝ ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገነኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት አምባሳደሮችም ፌስቲቫሉ የአገራትን ጥበብና ባህል ለማስተዋወቅና ቀጠናዊ ገፅታን ለመገንባት ስለሚጠቅም ወቅታዊ መረጃዎችን በመለዋወጥ አስፈላጊውን ተሳትፎ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.