Fana: At a Speed of Life!

የምግብና እርሻ ድርጅት ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓት ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ የግጭት ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች ለሚኖሩ 620 ሺህ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓት ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አስታውቋል፡፡
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት የአፍሪካ ሕብረትና የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ቺሚምባ ዴቪድ ፊሪ እንደገለጹት÷ ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስትን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው፡፡
በተለይም መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ድርጅቱ ይደግፋል ብለዋል።
በዚህም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓት ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፥ የግብርና ሰብል ምርታማነት የበለጠ እንዲያድግ ተጨማሪ ድጋፎችን ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
የእንስሳት ሀብት ልማት እንዲያድግም የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል ክትባቶችን ያቀርባል ያሉት ቺሚምባ ዴቪድ ፊሪ፥ ድጋፉን ለማቀላጠፍ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በእስካሁኑ ሂደት፥ በትግራይ ክልል ለሚገኙ 230 ሺህ አርሶ አደሮች 400 ሜትሪክ ቶን፣ በአማራ ክልል 100 ሜትሪክ ቶን እንዲሁም በአፋር አራት ሜትርክ ቶን ዘር አድርሷል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንስሳትን ከበሽታ ከመከላከል አኳያም በትግራይ ክልል ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን እንስሳት ክትባት መሰጠቱን ጠቁመው÷ በአፋር ክልል ደግሞ 230 ሺህ ለሚሆኑ እንስሳት የጤና አገልግሎት ተደራሽ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ድርጅቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለእነዚሁ አካባቢዎች የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑን የገለጹት ቺሚምባ ዴቪድ ፊሪ፥ 6 ሺህ 700 ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸው በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈጸም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በመንግስት በኩል የተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አርሶ አደሮች ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.