Fana: At a Speed of Life!

ምናባዊ ንብረት (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ህገ ወጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠብ ብሄራዊ ባንክ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን እንዲጠብቅ ባንኩ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ የገንዘብ መደብ ብር እንደሆነና በብሔራዊ ባንክ በሌላ አኳኋን ካልተፈቀደ በስተቀር በሀገሪቱ የሚከናወኑ ማናቸውም የገንዘብ ግንኙነቶች ሁሉ የሚከፈሉት በብር እንደሚሆን የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 በግልጽ እንደሚደነግግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 መሠረት በየትኛውም የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድም ሆነ ሥርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም፡፡

ነገር ግን ከጥናት ለመረዳት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት ከህግ እውቅና ውጪ የክሪፕቶ ከረንሲ፣ እንደ ቢትኮይን እና የመሳሰሉት የምናባዊ ንብረት (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) አገልግሎት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መጥቷል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም ይህ ተግባር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት እና በተለይም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ለማሸሽ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል ነው ያለው ባንኩ፡፡

ይህ እየተስተዋለ ያለው ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብን) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል ብሏል ባንኩ፡፡

በመሆኑም ይህን ፈጽመው በሚገኙ አካላት ላይ ብሔራዊ ባንክ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የገለጸ ሲሆን፥ ህብረተሰቡም ይህንን ህገወጥ ተግባር የሚሠሩ አካላትን ሲመለከት ለብሔራዊ ባንክ እና ለሚመለከታቸው ሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.