Fana: At a Speed of Life!

ከ110 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ሳምንት 110 ሚሊየን 66 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
 
ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ባደረገው ክትትል ነው 87 ነጥብ 9 ሚሊየን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 22 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች የተያዙት፡፡
 
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ፥ በቅደም ተከተላቸው 25 ነጥብ 1 ሚሊየን ፣ 12 ነጥብ 8 ሚሊየን እና 12 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻላቸው ተገልጿል ፡፡
 
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት ፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
 
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ እና ጥቆማ የተያዙ ሲሆን፥ ኮንትሮባንድ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሰባት ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የኮንትሮባንድ ድርጊትን ለመግታትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከልም ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.