Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ ሰራዊት ድባጤ ወረዳ የሚገኘውን የሸኔ ማሰልጠኛ ካምፕ አወደመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሰራዊት በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ የሚገኘውን የሸኔ ማሰልጠኛ ማውደሙን ኮሎኔል መኮንን ፀጋዬ ገለጹ፡፡

ኮሎኔሉ እንደገለፁት ÷ ከሚያዝያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም  ጀምሮ ሰራዊቱ ባከናወናቸው ተግባራት በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ቦንፎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የሸኔ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በማውደም 43 የሸኔ አባላት ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን÷ 60 የሸኔ  አባላት ደግሞ በሰላም እጃቸውን ሰጥተዋል።

በዚህም አሸባሪው ሲጠቀምባቸው የነበሩ 184 ኋላቀር መሳሪያዎች፣ 23 ክላሽንኮቭ፣ ከ300 ኩንታል በላይ በቆሎ፣ 16 ኩንታል አኩሪ አተር፣ ሁለት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ (ሶላር)፣ ሁለት የእህል ሚዛን እና ሁለት ማዳበሪያ አደንዛዥ ዕፅ መያዙን ኮሎኔል መኮንን  አብራርተዋል።

አሸባሪው ሸኔ ከህብረተሰቡ ዘርፏቸው የነበሩ 47 የቀንድ ከብቶችና 60 ፍየሎችንም ማስመለስ መቻሉን ነው ኮሎኔል መኮንን የገለጹት።

ለሦስት ዓመታት በድባጢና በቡለን ወረዳዎች በሸኔና  ፅንፈኛ ታጣቂዎች ስር የነበሩ 4 ቀበሌዎችም ነፃ መውጣቸውንም ተናግረዋል።

የድባጤ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ዋወያ በበኩላቸው እንደተናገሩት÷ በተገኘው አንፃራዊ ሰላም ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው በመመለስ ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ከመከላከያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.