Fana: At a Speed of Life!

የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠነቀቀ፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ÷ በሲሚንቶ ገበያ ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለማስተካከልና ገበያውን ለማረጋጋት በክልሉ ከሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤቶች ጋር ተወያይቶ ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውሷል፡፡
በዚህም መሠረት ሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ተደራጅተው ከመንግስት ፍቃድ ላገኙ ማኅበራት ምርታቸውን በማቅረብ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያከፋፍሉ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሲሚንቶ ገበያ ዋጋን ለማረጋጋት በሚያደርገው ጥረት እንቅፋት ለመሆን የሚሞክሩ አካላት እየተስተዋሉ መሆኑን በመግለጫው ጠቅሶ፥ በእነዚህ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
በመሆኑም ማንኛውም አካል ሲሚንቶ በሕገ ወጥ መንገድ አከማችቶ ከተገኘ፣ እንዲሁም ከተቀመጠው ዝርዝር ዋጋ ውጭ ሲሸጥ ከተደረሰበት ንብረቱ በመንግስት ተወርሶ፥ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንደሚከፋፈል ማስታወቁን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመልክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.