Fana: At a Speed of Life!

የመተከል እና የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አጎራባች ወረዳዎች ባህላዊ እርቀ ሰላም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ1፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የመተከል እና የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አጎራባች ወረዳዎች ሶስተኛው ዙር ባህላዊ እርቀ ሰላም ተካሂዷል፡፡

በማንዱራ እና ጓንጓ ወረዳዎች የሚገኙት የጨረቃ፣ ባሁስት፣ ዳች ሉምቢያ፣ ዳኋ ማክሰኚት፣ ባቢሳ ቀበሌ ነዋሪዎች እንዲሁም የሁለቱ ወረዳ የፖለቲካ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ነው ባህላዊው እርቀ ሰላም በጨረቃ ቀበሌ የተፈፀመው።

የጓንጓ ወረዳ የመተከል አዋሳኝ የሆነችው የጨረቃ ቀበሌ በ2013 ዓ.ም እና በ2014 ዓ.ም በጸረ-ሠላም ኃይሎች የተፈናቀሉ ከ3 ሺህ 300 በላይ ሰላማዊ የጉሙዝ ማህበረሰቦች ተጠልለው የቆዩበት ሲሆን÷ አካባቢውን ሲጠብቁ ለነበሩ የማንዱራ ወረዳ የዳች ሉምቢያ እና ዳኋ ማክሰኚት ነዋሪ ለሆኑት ለአቶ ሉምቢያ ረታ እና ዳዬ ከንቲባ እንዲሁም ለጨረቃ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ዋለልኝ አዲስ የሰላም አምባሳደርነት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በእለቱ የተገኙት የማንዱራ ወረዳ የዳች ሉምቢያ ነዋሪ የጉሙዝ ማህበረሰብ ተወካይ አቶ አዳሙ ዘለቀ”እኔ የማውቀው ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች መሆናችንን ነው” ብለዋል፡፡

የጓንጓ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው በበኩላቸው÷ “ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ የተፈጸመው ህዝባዊ እርቀ ሰላም ያለፈውን መጥፎ ጊዜ እያነሳን የምንወቃቀስበት ሳይሆን ፍፁም እረስተን ለወደፊቱ ሰላም እና ልማት ላይ አተኩረን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የምንጀምርበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ያለፈው ግጭት የተከሰተው በውጫዊ ሀይሎች ግፊት እና ጥቂት ተላላኪዎች እንጂ ህዝብ ከህዝብ ጋር ምንም ጸብ እንደሌለው በመጠቆም፥ ሁሉም የእርቀ ሰላሙ ታዳሚዎች የሰላም ባለቤት ሆኖ ወደ ልማት መመለስ አለበት ማለታቸውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.