Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ መስፈርቱን ላሟሉ ስምንት አዳዲስ ባንኮች ፈቃድ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ መስፈርቱን ላሟሉ ስምንት አዳዲስ ባንኮች ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል።
 
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳሬክተር ፍሬዘር አያሌው÷በፋይናንስ ዘርፉ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ለውጦችን ተከትሎ በርካታ ባንኮች የመመስረቻ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ባንክ ለመመስረት የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የካፒል መጠንን ከ500 ሚሊየን ወደ 5 ቢሊየን ብር ከፍ ማድረጉን አስታውሰው÷ አጠቃላይ መስፈርቱን ላሟሉ ፈቃድ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
በዚህ መሰረት የመመስረቻ ፈቃድ ከጠየቁ 25 አዳዲስ ባንኮች መካከል ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መስፈርት አሟልተው ለተገኙ 8 ባንኮች ፈቃድ መስጠቱን ተናግረዋል።
 
በብሄራዊ ባንክ ፈቃድ ካገኙ ስምንት ባንኮች በተጨማሪ 3 ባንኮች ፈቃድ የማግኘት ሂደቱን እያጠናቀቁ ሲሆን÷ ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
 
ብሔራዊ ባንክ ከቅድመ ማመልከቻ ሂደት ጀምሮ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸው ÷ የምስርታ ሂደቱ ካልተሳካ ለባለአክሲዮኖች ገንዘባቸው ተመላሽ ይሆናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በተመሳሳይ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ በ2012 ዓ.ም ብሄራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሰረት መስፈርቱን ያሟሉ 3 አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ባንክ መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።
 
ሌሎች ሁለት አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ደግሞ መስፈርቱን አሟልተው ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ለ28 ባንኮች ፈቃድ መስጠቱ ታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.