Fana: At a Speed of Life!

የወጪና የገቢ ንግድ ለማሳለጥ የተለያዩ የወደብ አገልግሎት አማራጮችን ለመጠቀም እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድ ለማሳለጥ የተለያዩ የወደብ አገልግሎት አማራጮችን ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ያብባል አዲስ ÷የብረትና ከሰል ምርቶች በታጁራ ወደብ በኩል ወደ አገር እንዲገቡ መደረጉም በጅቡቲ ወደብ ላይ የነበረውን መጨናነቅ እንደቀነሰው ተናግረዋል።

ለአንድ አገር የተሻለ የሎጅስቲክ አፈፃፀም የወደብ አማራጮችን መጠቀም በመሠረታዊነት የሚታይና የወጪና ገቢ ንግዱን የሚያሳልጥ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ÷ኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ ያላትን ዝቅተኛ የሎጅስቲክስ ደረጃ ለማሻሻል በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተተገበሩ ነው ብለዋል።

የሎጂስቲክ አፈጻጸምን ለማሻሻል በአማራጭ የወደብ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመው÷አማራጭ ወደቦችን መጠቀም በወደቦች የሚኖረው መጨናነቅ በመቀነስ የአንድ ወደብ ጥገኝነትም እንዳይኖር ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲጠቀም ከነበረው የጅቡቲ ወደብ ጎን ለጎን የታጁራ፣የበርበራና የሞምባሳ ወደቦችን መጠቀም መጀመሩን ገልጸዋል።

የወደብ አማራጮችን መጠቀም በጅቡቲ ወደብ ላይ የነበረውን የእቃ ክምችት በማቃለልና የሎጂስቲክ ሥርዓቱን በመሳለጥ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ነው ያስረዱት።

የብረትና ከሰል ምርቶች በታጁራ ወደብ እንዲመጡ መደረጉም በጅቡቲ ወደብ ላይ የነበረውን መጨናነቅ እንደቀነስም ጠቁመዋል።

በዚህም በኮሪደሩ መነቃቃት የፈጠረበትና የኮሪደሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻሎችን እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በታጁራ አማራጭ ወደቡ መጠቀም መቻሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል ፤ በተጓዳኝም በጋራ ወደቦችን በማልማት ከጎረቤት አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በ10 ዓመት መሪ እቅድ የአገሪቱን ገቢና ወጪ ጭነት አሁን ካለበት 17 ነጥብ 732 ሚሊዮን ቶን ወደ 30 ነጥብ 41 ሚሊዮን ቶን ከፍ ለማድረግ መታቀዱን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.