Fana: At a Speed of Life!

የወተት መሸጫ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የወተት መሸጫ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጨመሩን የአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅሬታቸውን ያቀረቡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፥ ከወተት ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ጥራት ያለው ወተት ማግኘት ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈታኝ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ አካባቢዎችም የወተት ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱንና የጥራት ጉድለት እንዳለም ነዋሪዎቹ ያነሳሉ።

ለዋጋ ንረቱ እና ለወተት ጥራት ጉድለቱ መከሰት የእንስሳት መኖ በሚፈለገው ደረጃ በገበያ ላይ ያለመኖር ምክንያት እንደሆነ የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ራሄል ነገሮ ገልጸዋል፡፡

የወተት ምርት ችግር እንዲቀረፍ እና ዋጋውንም ለማረጋጋት መኖ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኦሮሚያ ክልል የገበሬውን ሕይወት የሚለውጡ ሥራዎችን በሠፊው እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አርብቶ አደሩም ጥራት እና ብዛት ያለው የወተት ልማት ላይ እንዲያተኩር እና በገቢም ራሱን ጠቅሞ ኅብረተሰቡን እንዲጠቅም ሁኔታዎችን እያመቻቸን ነው ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የወተት ኃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አስመላሽ በርሄ በበኩላቸው፥ የወተት ዋጋ መጨመር ጊዜያዊ መሆኑን ጠቅሰው በጥራት እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ወተት ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው እንዲደርስ ሊጸድቅ የተዘጋጀ አዋጅ መኖሩን አመላክተዋል።

አዋጁ ሲጸድቅም የወተትን ደረጃ እና ጥራትን በዘላቂነት ለማስጠበቅና ለመቆጣጠር እንደሚረዳም ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል ወተትን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀለቀል ወደ ገበያ የሚያወጡ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የኅብረተሰብ አካላትን አዲስ በሚወጣው ህግ እና መመሪያ መሠረት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ነው የተመለከተው፡፡

በሲሳይ ጌትነት

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.