Fana: At a Speed of Life!

በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጎልበት የሕገ- መንግሥትን የበላይነት ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጎልበት የሕገ- መንግሥትን የበላይነት ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻ እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ዛህራ ሁመድ ገለጹ፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት የኦሮሚያ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የሲዳማ ክልል የጎንዮሸ መንግሥታት ግንኙነት የጋራ መድረክ በሐዋሳ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ዛህራ ሁመድ እንደገለጹት÷ በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጎልበት የዜጎች የመኖር መብት እንዲከበር፣ የጋራ እሴት እንዲዳብር፣ መቀራረብ እንዲፈጠር፣ በጋራ መበልጸግ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ይረዳል ብለዋል፡፡
ከዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ጎን ለጎን ሕዝቦች ለዘመናት ያካበቱትን ማህበራዊ መስተጋብር በማጎልበት በጋራ የመኖር እሴት እንዲዳብር የማድረግ፣ ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓት እንዲስፋፋ እና አብሮ የመልማትና የመሥራት ባህል ላይ ማተኮር ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በፌዴራል ስርዓቱ ላይ የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር በሕዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከርና በጋራ የመኖር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ተቋማዊ አሰራሮችን ማበልጸግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አራቱ ተጎራባች ክልሎች ለበርካታ ዘመናት አብረው የኖሩ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር ያላቸው፣ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተሳሰሩ፣ በርካታና እና ድንቅ የጋራ እሴት ባለቤት እንዲሁም ጠንካራ የስነ ልቦና ቁርኝት ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውንም አስታውሰዋል ምክትል አፈጉባኤዋ፡፡
ይህንን የመንከባከብ፣ የማሳደግና፣ ስር እንዲሰድ የማድረግ የማስተዋወቅ እንዲሁም እውቅና የመስጠት ሥራ ችላ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እና ከሲዳማ ክልል የተውጣጡ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች መሳተፋቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.