Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ ከተማ አገር አቀፍ የባህል እሴት ኮንፈረንስ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ “የባህል እሴቶቻችን ለዜጎች ስብዕና ግንባታ “በሚል መሪ ሀሳብ አገር አቀፍ የባህል እሴት ኮንፈረንስ ተካሄደ፡፡
ኮንፈረንሱን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ጋር በትብብር ያዘጋጁት ሲሆን÷ በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ባህላዊ እሴቶች የብሔር ብሔረሰቦች ሀብት ብቻ ሳይሆኑ የአንድነት መሰረት እና የኢትዮጵያ ሀብት እንደሆኑ ተናግረዋል።
በዓለማችን ላይ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የእድገት ደረጀ ላይ የደረሱ ሀገራት ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በአግባቡ መጠቀማቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጰያውያንም ከዚህ ትልቅ ትምህርት መውሰድ አለባቸው ብለዋል።
በሃገር አቀፍ ኮንፈረንሱ ላይ የባህል እሴቶች ለወጣቶች ስብዕና ግንባታ ያላቸው ሚና፣ የስራና የቁጠባ ባህልን ለማጠናከር የማህበረሰቡ ሚና ምን መሆን እንዳለበት እና የህብረተሰቡ ድርሻና የወደፊት አቅጣጫን በሚመለከት ጥናታዊ ፅሁፎች በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና በተጋባዥ እንግዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች ከባህል አንፃር ብዙ አስተማሪ የሆኑ ትምህርት የሚወሰድባቸው ብሎም ዜጎች ሊማሩባቸው የሚችሉና ስብዕናንም ሊቀርፁ የሚችሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በጋራ በመመካከርና በመተጋገዝ ለብልፅግና ጉዞ የስራ ባህልን ማሻሻል፣ ሀብት ፈጥሮ የቁጠባን ባህል ማዳበር እንዲሁም የባህል እሴቶችን አጉልቶ ለማውጣት የሚያስችል ኮንፈረንስ መሆኑን የገለጹት ደግሞ÷ የድሬዳዋ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ ናቸው።

በነስሪ ዩሱፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.