Fana: At a Speed of Life!

አለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ የልማት ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ ድጋፍ እንዲያደርግ እና የሀብት ማሰባሰብያ መንገዶችን በመቀየስ የልማት ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የገንዘብ ሚንስትር ዲኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ጠየቁ።

ሚንስትር ዴኤታዋ ከአለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በኮርፖሬት አገልግሎት ዲፓርትመንት ኃላፊ ጉኪ ዉ ከተመራው ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ መንግስት የተነደፉ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ፣ የፋይናንስ እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን በመክፈት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የተደረጉ ማሻሻያዎችን አድንቀዋል።

ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በብሔራዊ የገጠር ልማት እና በምግብ ዋስትና በኩል እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አብራርተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ መንግስት እና በአይፋድ መካከል ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀውን የስራ ግንኙነት አስታውስው፥ ፈንዱ በአሁኑ ወቅት 240 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገባቸውን ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ድጋፉን ከፍ ለማድረግ እና አዳዲስ የሀብት ማሰባሰብያ መንገዶችን በመቀየስ የልማት ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.