Fana: At a Speed of Life!

ነፃ የንግድ ቀጠና በድሬዳዋ ለማስጀመር የሚያግዝ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የብሄራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የፌደራል አመራሮች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለማስጀመር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከድሬዳዋ ካቢኔ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ነፃ የንግድ ቀጠናው ድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ወደ አገልግሎት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህም እንደ ሀገር የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነትን ትርጉም ባለው መልኩ ሊለውጥ የሚችል መሆኑን ጠቅሰው የሀገራችንን የገቢና ንግድ ስርዓት በማሳለጥ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች በበኩላቸው መንግስት በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመመስረት መነሳቱ ለማሳካት ለታሰበው የኢኮኖሚ ሪፎርም አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆኑ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እና የካቢኔ አመራሮች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመመስረት መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው ለተግባራዊነቱ ከፌደራል አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.