Fana: At a Speed of Life!

ተመድ ተፈጸሙ በተባሉ ጥሰቶች ላይ ሊያደርገው ያቀደው ተጨማሪ ምርመራ ተቀባይነት የለውም – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተመድ ተፈጸሙ በተባሉ ጥሰቶች ላይ ሊያደርገው ያቀደው ተጨማሪ ምርመራ ተቀባይነት እንደሌለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና በመንግስታቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የጋራ ሪፖርት ላይ የተመላከቱ ምክረ ሀሳቦችን ለመተግበር መንግስት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ነገር ግን በተመድ በኩል ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የሚደረገው አካሄድ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ አገራዊ ምክክሩ በሂደት ላይ መሆኑ እና ሰላምን የማስፈን ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።

ህወሓት ለሰላም ጥረቶች በጎ ምላሽ እየሰጠ እንዳልሆነ እና ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህንንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ጠይቀዋል ቃል አቀባዩ።

ወደ ትግራይ የሚሄደው ሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ቃል አቀባዩ፥ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅሞች ባስጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተመራ ልዑክ በሶማሊያ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ላይ መገኘቱን ጠቅሰው፥ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማሳደግ ለቀጠናው ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከበርካታ የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን በማንሳትም፥ ለአሜሪካ የኮንግረስ አባል፣ ለአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ እና ለሌሎችም በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የኪነ ጥበባት እና የባህል ፌስቲቫል በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የጠቀሱት አምባሳደር ዲና፥ ፌስቲቫሉ በቀጠናው አገራት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር እድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።

ከውጭ ግንኙነት ጋር በተያያዘም የሀገራት ግንኙነት ተለዋዋጭ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፥ ከአረብ ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት ታሪካዊ እና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ እንደመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል በመግለጫቸው።

የህዳሴ ግድብ ትርክት በተሳሳተ መልኩ በመቅረቡ ከአረብ አገራት ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተወሰኑ እጥረቶችን ቢፈጥርም ሁኔታዎችን ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግም አውስተዋል።

ከሱዳን ጋር ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻርም ሱዳን የኢትዮጵያን መሬቶች ያለ አግባብ መያዟን በመጥቀስ፥ ሆኖም ኢትዮጵያ የሱዳንን ጉዳይ የያዘችበት መንገድ አዋጭና ሰላማዊ መሆኑን ገልጸዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.