Fana: At a Speed of Life!

እየተወሰደ ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ነው -የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) እየተወሰደ ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያ ክልል በሸኔ የሽብር ቡድን ላይ በተወሰደው እርምጃ በኦሮሚያ ክልል አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን እና በሽብር ቡድኑ ይዞታ ስር የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቅ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ በክልሉ ሰላም መስፈኑን አስረድተዋል።

ከህግ ማስከበሩ ጎን ለጎንም የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።

መንግስት መዋቅሩን እያፀዳ የህግ ማስከበር እርምጃወችን እየወሰደ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ የህግ ማስከበር ዘመቻው አሁንም አላለቀም ብለዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በተለያዩ ወንጀሎች ተሳታፊ የነበሩ ግለሶቦችን በተለይም በኮንትሮባንድ እና በሽብር ተግባራት ሲሳተፉ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም ነው የገለጹት።

በሶማሌ ክልል ይንቀሳቀስ የነበረው አልሸባብ ጥቃት ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ቀድሞ በመታወቁ የሽብር ቡድኑ ሊያደርስ የነበረውን ጥቃት ቀድሞ ማስቀረት መቻሉንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል፡፡

የሰብዊ ድጋፍን በተመለከተም በሀገሪቱ በአጠቃላይ 11 ሚሊየን ለሚሆኑ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አንስተዋል፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ዞን፣በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በአፋር ክልል 3 ዞኖች ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖች የምግብ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልልም የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ እርዳታ ተቋማት ጋር በመተባበር እስካሁን በየብስ ትራንስፖርት 86 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍ ማድረጉንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል፡፡

ከምግብ በተጨማሪ የነዳጅ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በሁለት ወራት ብቻ 782 ሺህ ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ እያደረጉ ቢሆንም ነገር ግን በቂ አለመሆኑን አመላክተዋል፡፡

በቀጣይም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የአምባሳደሮች ጉብኝትና የምክክር መድረክ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ በአማራ እና አፋር ክልሎች በአሸባሪ የህዋሓት ቡድን የተፈፀሙ ወንጀሎች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ እና ህብረቱ በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ እንደሚያቀርብ አውስተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.