Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ አሻራ አራተኛን ዓመት ምክንያት በማድረግ በመላ ኢትዮጵያ የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ተደርጓል -ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አራተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመላ ሀገራችን የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ የ2014 አረንጓዴ ዐሻራ ሊጀመር መቃረቡን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ለመርሐ ግብሩ የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ6 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ ከ3 ቢሊየን በላይ የደን፣ ከ2 ቢሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ የጥምር ደን ችግኝ፣ ከ500 ሚሊየን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ፣ 35 ሚሊየን የቀርከሃና 800 ሚሊየን ደግሞ ለእንስሳት መኖ ጥቅም የሚሰጡ ቁጥቋጦዎች እና ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2013 ዓ.ም 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከለ ታቅዶ 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ መትከል መቻሉንና ባለፉት አመታት በተደረገ የችግኝ እንክብካቤ የጸደቃ ደረጃ ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሰው፥ አጠቃላይ የ3 አመቱ ተከላ አማካኝ ውጤት 80 ነጥብ 5 በመቶ የጽድቀት ደረጃ ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

በዘንድሮው መርሐ ግብርም ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ በቆላማ አካባቢዎች ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን በመትከል እንዲሁም በደጋማ አካባቢዎች እንደ ቀርከሃ፣ ዝግባና ኮሶ የመሳሰሉ ሃገር በቀል ዝርያዎችን መትከል እንደሚገባ ተገልጿል ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.