Fana: At a Speed of Life!

የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ነው- የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

“ሽብርተኝነትን በመከላከል የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ በጋራ እንጠብቃለን!” በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ÷ ሽብርተኝነት አገርና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ዓለም አቀፍ ስጋት በመሆኑ የመከላከል ተግባሩ ሁሉንም ይመለከታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የነበሩ የሽብር ድርጊቶችን በማክሸፍና በመከላከል ሂደት የተሳካ ስራ መሰራቱንም አስታውሰዋል።

በዚህ ተግባር አጠቃላይ የሕዝቡና የጎረቤት አገሮች አቻ ተቋማት የነበራቸውን ሚና አድንቀው÷ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኗን ያብራሩት ዳይሬክተሩ ÷ ሽብርተኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት ሆኖ የቀጠለ የጋራ ችግር በመሆኑ የጋራ መከላከልን ይጠይቃል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ወቅታዊ የሽብርተኝነት ስጋቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.