Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ላይ የሚሰራጩ ግጭት-ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮችን ፌስቡክ መቆጣጠር አለመቻሉን ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌስቡክ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን ኩባንያው መቆጣጠር አለመቻሉን ወይም አለመፈለጉን በማይናማር እና በኢትዮጵያ ላይ የተካሄደ ጥናት አመለከተ።

በፌስቡክ የተሰራጩ ግጭት ቆስቋሽ የጥላቻ መልዕክቶች በማይናማር ጅምላ ጭፍጨፋ ማስከተላቸውንና ኢትዮጵያም በፌስቡክ በኩል የተሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ሰለባ መሆኗን የተካሄደው ጥናት አብራርቷል።

ጥናቱን ያካሄዱት “ግሎባል ዊትነስ” እና “ፎክስ ግሎቭ” የተሰኙ ለትርፍ ያልተቋቋሙ የጥናት ተቋማት መሆናቸውንም ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡

በጥናታቸው ÷ ፌስቡክ እንደ ማይናማር ሁሉ ኢትዮጵያ ላይም ትኩረት አድርገው የጥላቻ መልዕክቶች እንደሚሰራጩ እና ኩባንያውም መቆጣጠር አለመቻሉን ነው ያረጋገጡት፡፡

አጥኚዎቹ የፌስቡክ የጥላቻ ንግግር መለያ ዘዴዎች ምን ያህል አስተማማኝ መሆናቸውን ለመፈተሽ ሆን ብለው ያዘጋጇቸው የጥላቻ ንግግር ይዘቶችን በማስታወቂያ መልክ እንዲያስኬድ ልከውለታል።

ነገር ግን ለፌስበክ እንደማስታወቂያ የቀረቡትን እነዚህን የጥላቻ ንግግሮች ኩባንያው እንደተቀበላቸው ገልጸው፥ ነገር ግን ጥናት አድራጊዎቹ መልዕክቶቹን ሳያስተላልፏቸው አንደቀሩ በጥናት ሪፖርቱ ተጠቁሟል።

እነዚህ በፌስቡክ ማስታወቂያ ሆነው መሄድ እንደሚችሉ የተፈቀደላቸው ይዘቶችም ሰዎችን እንዲገደሉ የሚቀሰቅሱ እና ሰዎችን ከእንሰሳት ጋር አመሳስለው የሚያስቀምጡ ስለመሆናቸው ነው የጥናቱ ሪፖርት የጠቆመው።

ይህ የጥናት ግኝት፥ ፌስቡክ የይዘትና የሥነ ምግባር አጠቃቀም መመሪያውን የሚጥሱ የጥላቻ ንግግሮችን ያዘሉ ማስታወቂያዎች በኢትዮጵያ እንዳይሰራጩ መከላከል እንዳልቻለም ማሳያ ነው ተብሏል።

በፈረንጆቹ 2021 ድብቅ መረጃዎችን በመፈልፈል እና በማጋለጥ የምትታወቀው ፍራንሲስ ኸውጋን በሰጠችው ቃል÷ ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮችን መቆጣጠር እንዳልቻለና በኢትዮጵያም ብሔር -ተኮር ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ የሚገፋፉ መልዕክቶች ያለአንዳች ከልካይ መሰራጨት መቀጠላቸውን እንደታዘበች ተናግራለች፡፡

የጥናት ቡድኑ ÷ ሰብዓዊነትን የሚነኩ ብሎ ከመደባቸው የጥላቻ መልዕክቶች መካከል ÷ የአማራ፣ የኦሮሞ እና የትግሬ ብሔር የሆኑ ግለሰቦች እንዲገደሉ በፅንፈኞች የተላለፉ ጥሪዎችን ጭምር መመልከቱን ነው የጠቆመው፡፡

በጉዳዩ ላይ “ሜታ” በሚል የንግድ ስያሜ የመጣው ፌስቡክ ኩባንያ ÷ የጥላቻ መልዕክቶቹ ከቁጥጥሩ አልፈው መሠራጨት እንዳልነበረባቸው አምኖ፥ በቀጣይ በተፈጠረው ጥብቅ የዲጂታል ስርዓት ቁጥጥር ስለሚደረግባቸው ችግሩ እልባት እንደሚያገኝ አስታውቆ ነበር ተብሏል፡፡

ኩባንያው ይህን ቢልም ቃል በገባ በሣምንቱ ሁለት ተጨማሪና ግጭት-ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮች ተጽፈው መሠራጨታቸው ነው የጠቀሰው፡፡
በዚሁ ምክንያት የፌስቡክ ሜታ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ሼሪል ሳንድበርግ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውንም ዘጋርዲያን አስታውሷል፡፡

ፌስቡክአሁንም የጥላቻ ንግግሮች መሰራጨታቸውን አምኖ፣ አማርኛን ጨምሮ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች የሚያውቁ ሠራተኞች እንዳሉት በመግለጽ ÷ ሰው በመሆናቸው ሊሳሳቱ ይችላሉ ብሏል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.