Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ነጻ ሆኖ ራሱን የሚያስተዳድር ዩኒቨርሲቲ ይሆናል- ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ ራሱን የሚያስተዳድር ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆን የትምህት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ሆኖ የመመራት መብት የሚሰጥበት የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሄዷል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ÷ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲን ተከትሎ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በሂደት ወደ ነጻ ዩኒቨርሰቲነት እንደሚቀየሩ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ውጪ በመሆን ነጻ ተቋም እንዲሆን የተወሰነውም መንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን በራስ ገዝ አስተዳደር እንዲተዳደሩ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሳው ወልደሃና “የዩኒቨርሲቲዎች በነጻ የመመራት ፈተና እና እድል” በሚል የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
በጽሑፋቸውም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ዩኒቨርሲቲዎች ነጻነታቸው ተጠብቆ የመምራት፣ ሰራተኛ የመቅጠር፣ተማሪን የመቀበል፣ ሃብት የማፍራትና የማስተዳደር፣ ከተቋማ ጋር በራስ ግንኙነትን በመፍጠር የሁለትዮሽ ስራን ማጠናከር፣ የራሳቸውን አቅም የሚፈቅደውን ደረጃዎችን ማውጣትና መሰል ተግባራትን መፈጸም እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ባለመሆናቸው ምክንያት ይህን ሁሉ ማድረግ አይችሉም ያሉት ፕሮፌሰር ጣሳው÷በዚህ ሳቢያም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በሚፈልጉት ፍጥነትና ጥራት ማከናወን አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በራስ የሚተዳደሩ ነጻ ተቋም ሲሆኑም አቅማቸውንና ብቃታቸውን ያገናዘበ ውሳኔዎችን በመወሰን የተሻለና አገር የሚጠቅሙ ተግባራትን ይከውናሉ ብለዋል።
ነጻ ዩኒቨርሲቲ እውቅናው በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ከዚህ ቀደም ባለው ልምድና የተሻለ አቅም ላይ የሚገኝ በመሆኑ ነው ተብሏል።
ነጻ ዩኒቨርሲቲ ማለት ከመንግስት ተመጣጣኝ በጀት የሚያገኝና ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጣቸው የነጻነት ስፋትን በአአግባቡ መጠቀማቸውን የሚቆጣጠር ሆኖ ከዛ ውጪ አንድ የግል ተቋም ሊያደርገው የሚችለውን ተግባር በሃላፊነት የማድረግ መብት የሚሰጥ ነው።
ከዚህ ባለፈም ተማሪዎችን በራሱ ፈትኖ መቀበል፣ ስኮላር ሺፕ መስጠት፣ የወጪ መጋራትን በራሱ አካሄድ መተግበር የሚችል፣ መምህራንን በፈለገው ጊዜ የሚቀጥር፣ በአቅሙ የሚከፍልና እርምጃም የሚወስድ፣ የፋይናንስ አስተዳደርን በራሱ የሚመራ እና ሌሎችም ተግባራትን በነጻነት የመከወንን መብት የሚሰጥ ነው ተብሏል።
በኃይለኢየሱስ ስዩም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.