Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ አስተዳደር የጎርፍ አደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4 ፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው ክረምት የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ አዲስ አበባ ከፈጣን ልማት፣ ከዘላቂ የዕድገትና የከተማ ማስዋብ እንቅስቃሴዎቾ በተጓዳኝ ለልዩ ልዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ስጋት የተጋለጠች ከተማ መሆኗን አንስቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ቢሮው አስፈላጊው ሁሉ ቅድመ ጥንቃቄ የወቅቶች መለዋወጥና የአየር ንብረት መዛባትን ተከትለው የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀልበስ በተቀናጀ መልኩ መደረግ አለበት ብሎ እንደሚያምን እና የድርሻውን ኃላፊነት ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር እንደሚወጣ አሳውቋል ።

ባለፉት ዓመታት ጐርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የቆሻሻ መደርመስና መሰል አደጋዎች በከተማዋ ማጋጠማቸውን ተከትሎ የከፋ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን መግለጫው አስታውሷል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት የክረምት ወራት በመዲናዋ የወንዝ ዳርቻዎች፣ በተዳፋት ቦታዎች፣ በረባዳማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው በመሆኑ፥ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ጥንቃቄ የአካባቢው ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት በጣምራ እንዲያርጉ ሲያሳስብ መቆየቱም ተጠቁሟል፡፡

ካለፉት ጊዚያት ልምድ በመውሰድ ከተማ አስተዳደሩ በመጪው የክረምት ወቅት መሠል አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ እንዳያጋጥም አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል፥ ከሚመለከታቸው ተቋማት የባለሙያዎች ቡድን በማዋቀር የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች የመለየት ሥራ በስፋት ማከናወኑ ተመላክቷል፡፡

በሁሉም ክ/ከተሞችና ወረዳዎች በባለሙያዎች በተደረገ የጥናት ውጤት መሰረት 161 አካባቢዎች በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ የአደጋ ስጋት ያለባቸው ሲሆኑ÷ ከእነዚህም መካከል ደግሞ 61 አካባቢዎች ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው እና ተጋላጭ አካባቢዎች መሆናቸው በተደረገው ጥናት መለየቱ ነው የተገለጸው፡፡

በጥናቱ ምክረ ሀሳብ መሰረት ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን የሰው ኃይልና በጀት በመደብ ስጋቱን ለማቃለል የሚረዱ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን አስቀድሞ ማከናወን መጀመሩም ተመላክቷል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወትና ንብረት ልከሰት የሚችልን የትኛውንም ድንገተኛ አደጋ ታሳቢ በማድረግ ፣ብሎም ስጋት አለባቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች በሚገኙ ልዩ ልዩ ተቋማትና በልማት አውታሮች ላይ ጉዳት እንዳያጋጥም ኢንዲሁም በልዩ ልዩ አደጋዎች ምክንያት በአጠቃላይ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ልደርስ የሚችልን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ የሚመለከታቸውን ተቋማት በማስተባበር አስቀድሞ በተደረገው ጥናት የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ዋቢ በማድረግ በአስተማማኝ ሁኔታ ስጋቶችን ለመቅረፍ እንዲቻል በርካታ ተግባራት በሚከተሉት አካባቢዎች በስፋት እየተተገበሩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

በዚህ መሰረትም በወንዝ ዳርቻ ወይም አቅራቢያ የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የማንሳት እንቅስቃሴ ፣ በወንዞች ዳርቻ የአፈር መንሸራተትና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ ግንባታዎችን የማከናወን ሥራ፣ በወንዞች ውስጥ የተጣሉ ቀሻሻዎችን በማንሳት የማጽዳት እንቅስቃሴ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን በአገር በቀል እጽዋት የመሸፈንና ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን የማፅዳት እንቅስቃሴ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን ወሰን ማስከበርና የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ የቅድመ መከላከል ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆናቸውን ቢሮው በመግለጫው አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.