Fana: At a Speed of Life!

የሲሚንቶ ግብይትን እያዛቡ ያሉት አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከግብይት ውጪ ተደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4 ፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲሚንቶ ግብይትን እያዛቡ ያሉት አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከግብይት ውጪ መደረጋቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በሰጡት መግለጫ÷በግንባታው ዘርፍ ዋነኛ ግብዓት የሆነው ሲሚንቶ ግብይቱ ኢኮኖሚያዊ ባልሆኑ ሰውሰራሽ ምክንያቶች እየተዛባ ዋጋውም ከጊዜ ወደጊዜ እየናረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
 
ለግብይቱ ችግር ውስጥ መውደቅ መንስኤ ከሆኑት ውስጥ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ዋነኛው መሆኑን ነው ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
 
በሀገራችን ካሉ 13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ውስጥ ከአንዱ በስተቀር እያመረቱ ያሉት ከማምረት አቅማቸው በአማካይ 50 በመቶ በታች መሆኑን ጠቁመው÷ ይህንን ለመሻሻል በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ውጤት ባለመምጣቱ በግብይቱ ላይ እየተስተዋለ ያለው ችግር ሊቀጥል ችሏል ብለዋል፡፡
 
የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆን፣ የመለዋወጫ እጥረት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመሟት የፋብሪካዎች ምርታማነት ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
 
በሀገራችን ባሉ በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶች ምክንያት የሲሚንቶ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የአቅርቦትና ፍላጎቱን ልዩነት ያሰፋው ሲሆን÷ይህም ግብይቱን ለምዝበራ ከመዳረጉ ባለፈ አምራቾችና አከፋፋዮች በፈጠሩት ቁርኝት በፋብሪካ ግቢ ውስጥ ያለ ደረሰኝ የሚፈጸሙ አላስፈላጊ ግብይቶች መኖራቸውና በዚህም ኢ-ፍትሃዊ የሲሚንቶ ስርጭት መፈጠሩ በጥናት መረጋገጡን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
 
ችግሩን በመፍታት የሲሚንቶ ምርት በተመጣጠነ ዋጋ ለተጠቃሚው ለማድረስም መንግስት የሲሚንቶ አከፋፋዮችንና ቸርቻረዎችን ከገበያ ውጪ እንዲሆኑ መወሰኑን አቶ ገብረ መስቀል አስታውቀዋል፡፡
 
የፌደራልና የከልል ፕሮጀክቶች ቀጥታ ከፋብሪካዎች ሲሚንቶ ገዝተው መጠቀም ይችላሉ እናበክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከተሞች ውስጥ ለፋብሪካዎች ሲሚንቶ ማከማቻ መጋዘን የሚዘጋጅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
 
ማንኛውምተጠቃሚዎና ፕሮጀክቶች በአቅረቢያቸው ከሚገኙት መጋዘኖች ሲመንቶን በፋብሪካ ዋጋ መግዛት እምደሚችሉም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
 
በሀገራችን የንግድ ህግ መሰረት ወኪል አከፋፋይ ስለማይፈቅድ የሲሚንቶ ወኪል አከፋፋዮችም በግብይቱ ውስጥ ሊኖሩ እንደማይፈቀድ ሚኒስትሩ መጥቀሳቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የፋብሪካዎች ምርታማነት ተሻሽሎ አቅርቦትና ፍላጎቱ ሲመጣጠን ለግብይቱ ሌላ መፍትሄ እንደሚበጅም ነው የተናገሩት፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.